ግጥሚያው

10 3 0
                                    


የጨዋታው ፍፃሜ - ክፍል አንድ

ሉሉ ብሎ /ጫቱን ተፍቶ/ ጨዋታውን የጀመረው፣ ነገር ግን አላስችል ብሎት እረፍት ሰዓት ላይ በጉንጩ [የበሻቱን ቂጥ የሚያክል] ግድንግድ ተርዚና ወጥሮ ተመልሶ የሁለተኛውን አጋማሽ ጨዋታ የመራው የመሃል ዳኛ ጉሮሮው እንደታነቀ ሰው አይኖቹን እስኪቀደዱ ድረስ በልቅጦ/በልጥጦ፣ ጉንጩን የወጠረው ተርዚናው ቀስበቀስ ሟሽሾ /ፈርሶ/ በምትኩ ትንሽዬ ከረሜላ አፉ ውስጥ የሸጎጠ የሚመስለውን /እንደውም በይበልጥ በስንትና ስንት የውሃ እናት ደረቷን አስነክሳ፣ የእውነት ይሁን ወይም ሰውነቷ በአለርጂክ ተቆጥቶ፣ ብቻ ደረቷ ላይ እብጥ ያለች፣ ኪንታሮት የምታክል የጡት ቅንጣቢ የሚመስለውን/ ጉንጩን በትፋሹ ሞልቶ በsilcon የተሞላ ወተት ቤት አስመስሎ ወጥሮ፣ አፉ ላይ ሰክቶት በምርቃና እንደጡጦ የሚመጠምጠውን እና በነፋው ቁጥር የታኘከ ጫት ከተርዚናው እየተገመሰ ወደውስጡ እየገባ ተጠቅጥቆበት የሚወደውን ሰው ቀብሮ እንደተመለሰ ሰው /እንደ ሀዘንተኛ/ ድምፁ የታፈነውን፣ ነገር ግን ባለንብረቱ /ባለቤቱ/ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ወዲያውኑ በፍጥነት እንዲመልስለት አስምሎና አስገዝቶ  /አስጠንቅቆት/ [ምን ነካችሁ እዛ ሰፈር እኮ ጀበናም አፍንጫዋን አታምንም] ሲሰጠው ድምፁ ከሜዳው አልፎ መንገድ ላይ የሚመላለሱትን ተሽከርካሪዎች ሾፌሮችን ያስበረግግ የነበረውን ፊሸካ አንገቱ ላይ ያሉት ደምስሮች እየተገታተሩ በትግል ነፍቶ የመልስ ጨዋታውን ፍፃሜ አበሰረ።

ይሄ ሁሉ ግን [ፊሽካ] ለመንፋት ነው? አልበዛም እንዴ!

[ለማንኛውም...]

ጨዋታው በባለሜዳው ቡድን 3 ለ 1 [፣በደርሶ መልስ 5 ለ 3] ተጠናቀቀ።

የፊሽካውን ድምፅ ተከትሎ የቡድኑ በረኛ የሆነው ማህደር እንደ እብድ እየጮኸ እና በዘለግላጋ ቁመቱ እየዘለለ፣ መሃል ሜዳው አካባቢ ሆኖ በደስታ ሰክሮ በእጆቹ አየሩን በቡጢ ወደሚነርተው፣ በእለቱ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሶስት ግቦች/ጎሎች የመጨረሻዎቹን ሁለት ግቦች ወዳገባው የቡድኑ አጥቂ ወደሆነው ዛክ በረረ።

ማህደር እንደደረሰ ዛክን ከኋላው በኩል፣ እጆቹን በሽንጡ ዙሪያ ጠምጥሞ ይዞት ወደላይ አንጠለጠለው።

ማህደር የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ከየት እንደተነሳ በማይታወቅ፣ እንደ ጋዛ ሮኬት እየተምዘገዘገ መጥቶ ከመሃል አናቱ ትንሽ ዝቅ ብሎ ጭንቅላቱ ላይ ባረፈው ኢላማውን የጠበቀ የድንጋይ ሮኬት ምክንያት የተፈነከተው ጭንቅላቱ ላይ ለሳምንት ያክል ተለጥፎ የነበረው ፋሻ መውደቁን እንኳን አላስተዋለም።

በፋሻው ተሸፍኖ የነበረው ፍንክቱ አካባቢ ያለው፣ ለብቻው ዙሪያውን በሰፊው የተላጨው ፀጉር እንደገና ማደግ/ማቆጥቆጥ ጀምሯል። ነገርግን ጭንቅላቱን በደንብ ለተመለከተው አብዛኛውን ጊዜ የክንፍ መስመሩን በጣም ተጠግተው፣ ሜዳውን ዙሪያውን ከበው የሚመለከቱትን ነውጠኛ ደጋፊዎች ሽሽት ሁሉም ተጫዋቾች ወደ መሃል ስለሚሳቡ/ስለሚጠጉ፣ ከሌላው የሜዳው አካል በተለየ ሳሩ የበለጠ ሳስቶና ደርቆ አመዳም የሆነውን/የሚመስለውን የኳስ ሜዳውን የመሃል ሜዳ አካባቢ ይመስላል።

" ዛካካካ!... ይሄን ነበር የምልክ፣ yes-ssss!" ማህደር እየጮኸ ዛክን ከጀርባው በኩል ወገቡን ጥፍር አድርጎ ይዞ እንዳንጠለጠለው፣ ወደላይና ወደታች፣ ከዛ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ደጋግሞ ነቀነቀው።

ዛክ በንቅናቄው ምክንያት ቃላቶቹ እየተቆራረጡ "Yes-sss, Ye-ey-y-" ብሎ ቡጢ የጨበጠውን እጁን አያነቃነቀ/እያወዛወዘ፣ እንደተንጠለጠለ አብሮት ጮኸ።

ማህደር፣ "ዛካ.. እንደው ምን ላድርግህ? ምን ልሁንልክ፤ ላንተ ብሞትልክ እራሱ ቅንጣት ታክል አይቆጨኝም!" ብሎ፣ ዛክ በለበሰው ውሃ ሰማያዊ ማልያ ላይ በጥቁር ቀለም በተፃፉት ሁለት '1' /'11'/ ቁጥሮች አናት መካከል የሚገኘውን ጀርባውን በስሱ በፍቅር ንክሻ ነከሰው።

ዛክ ፊቱ በፈገግታ ታጅቦ፣ ከንክሻው እራሱን ለማስመለጥ፣ ከደረቱ ወደፊት ተስቦ ተወራጨ።

ከመጠን በላይ ተደስቷል፤ መላው ቡድኑም፣ የመንደሩ ሰዎችም እንደዛው። ለምን አይደሰቱ? ክረምቱን ሙሉ ከስንት የድንጋይ ናዳ እና የዱላ ውርጅብኝ ተርፈው የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል።

በዛ ላይ ደግሞ ሽልማቱ እኮ


ጠብደል ፍየል ነው! ---

አዎ! ፍየል!

ሊያውም ምን የመሰለ:

ሸበላ የቀይ ዳማ፣

እንደ ጣቃ/ቦንዳ/ ጥቅጥቅ ያለ፣

ቆለጡ ተቀጥቅጦ የተኮላሸ ድንግል፣

ፀጉሩን የተላጨ አንበሳ የሚመስል፣

ግድንግድ ጠብደል፣

ፍየል!

* * *

የዚህን አድለ ቢስ ፍየል መጨረሻ...

እባክዎን ክፍል ሁለትን ቀጥሎ ያንብቡ

Green SparklesWhere stories live. Discover now