የግጥሚያው ፍፃሜ ክ2

8 3 0
                                    


የቡድኑ ኮች የክንፍ መስመሩ አካባቢ በዙሪያው ክብ ሰርተው ቁጢጥ ያሉትን/squat/ የተቀመጡትን ተጫዋቾች ከጨዋታ በኋላ የተለመደውን፣ ካሸነፉ በጣም አጭር የሆነውን ከተሸነፉ ግን ሰዓታት የሚፈጀውን፣ ንግግሩን ፊቱ በደስታ እንደበራ፣ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው።

ሆኖም ግን ሁሉም ሃሳባቸው ያሸነፉት ፍየል ላይ ነው።

በህብረት እየጨፈሩ ወስደው፣ ወዲያው ሰውተውት፣ በብረት ምጣድ አሳምረው ጠብሰው፣... በህብረት እስከሚመገቡት ጓጉተዋል።

ማህደር ቁጢጥ እንዳለ እጆቹ ላይ ያሉትን ጓንቶች ተራ በተራ ፈትቶ ካወለቀ በኃላ ግራ እጁን አጠገቡ የነበረው የቡድኑ ጨዋታ አቀጣጣይ የሆነው ሳሚ ትከሻ ላይ ተደግፎ ተመቻቸ።

ሳሚ የመጀመሪያውን ግብ በሚገርም ጥበብ ነበር ያስቆጠረው።

አየር ላይ ወደ እርሱ የመጣችውን ኳስ ጀርባውን ለተቃራኒው እንደሰጠ በደረቱ አብርዶ፣ ከኋላው በነበረው ተከላካይ አናት ላይ አሳልፎ፣ ተከላካዪ ሲደናበር እሱ በፍጥነት በጎኑ በከል ዞሮ ካለፈው በኋላ የምትነጠረውን ኳስ አብርዶ፣ ብቻውን የቀረው ግብ ጠባቂ እራሱን ለማግዘፍ እጆቹን ወደጎን በረዥሙ ዘርግቶ እና እግሮቹን በርግዶ ጆፌ አሞራ አክሎ በቆመበት ኳሷን በተበረገዱት እግሮቹ አቅጣጫ መሬት ለመሬት መታት።

ግብ ጠባቂው እግሮቹን ሲከድን ኳሷ አልፋው መረቡን ነክታለች፤ በሃዘን ጭንቅላቱን ይዞ እዛው ባለበት ወደኋላ በጀርባው ዘፍ ብሎ ተንጋለለ።

ሳሚ ማልያዋን አውልቃ፣ አየር ላይ እያሽከረከረች ችኮች በብዛት ተከማችተው ጨዋታውን እየተመለከቱ ወዳሉበት አካባቢ አቅጣጫ ከነፈች።

ነገር ግን የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ቡድኑ እየተጠቃ ስለነበር፣ የተቃራኒው ቡድን ብቸኛዋን ጎል ሲያስቆጥርባቸው የነበራቸውን የአንድ ጎል ብልጫ ለማስጠበቅ በማሰብ፣ ሳሚ በአካል ከሌሎቹ ደቃቃ በመሆኑ ኮች ወዲያውኑ ቀይሮ ስላስወጣው የሳሚ ፊት ላይ አሁንም ድረስ ኩርፊያ ይታይበታል።

ማህደር ሳሚን ተመለከተው። እንደተበሳጨ ሲገባው፣ የሳሚ ትከሻ ላይ ተደግፎበት የነበረውን እጁን በሳሚ ማጅራት አሳልፎ አቀፈውና፣ አድርጎት የነበረው ጓንት በፈጠረው ሙቀት ሙክሙክ ብሎ /soaked/ በላብ የወረዛው እና የተቀቀለ ድንች የመሰለው መዳፉ ላይ ባሉት እርጥብ ጣቶቹ በተቃራኒው በኩል ከጆሮው በታች የሚገኘውን የሳሚን ጉንጭ እያሻሸ፣

"ቅመሟ፤ አንቺም እኮ ዛሬ ምርጥ ነበርሽ። የእውነት፣ ናንዬን ይንሳኝ። [እሙሙ] አቆምሽ -መ-ሰ-ለ-ኝ--" አለው።

"ሂድ ወደዛ ባክህ፤ ይሄን 'እሙሙ' 'እሙሙ' የሚሸተውን እጅክን ከፊቴ ላይ ዞር አድርግልኝ።"

ሳሚ በመፀየፍ ፊቱን አኮማትሮ፣ ሰውነቱን ጉንዳን እንደወረረው ሰው አርገብግቦ /ተንዘፍዝፎ/ የማህደርን አይበሉባ /ከመዳፉ በታች ያለውን/ በጣቶቹ ጫፍ ይዞ ወደኃላ ገፋው፤ ማህደር ባላንሱን ስቶ ወደኋላ ሊወድቅ ሲል የሳሚን ትከሻ ጨምቆ ይዞ ጎተተው፤ መቋቋም ያቃተው ሳሚ ተከትሎት ወደኋላው ተፈነገለ፤ ቀድሞት መቀመጫው መሬት የደረሰው ማህደር ከኋላ ሲደግፈው እሱም በተራው መሬቱ ላይ በመቀመጫው ተዘረፈጠ።

ማህደር መሬቱ ላይ በተቀመጡበት ወደሳሚ ጆሮ አፉን እያስጠጋ፣ ዛክን ለአፍታ አይቶ/ገርምሞ/ አይኖቹን መለሰና በሹክሹክታ

" -- ነው ወይስ የባለግሮሰሪዋን ልጅ ዛክ መልሶ ተረከበሽ?" አለው።

ማህደር ሳምንቱን ሙሉ 'የባለግሮሰሪዋ ልጅ' እያለ ሲያደርቃቸው ነው የከረመው።

"አንተ ልፊያክን አቁም!..."  ኮች ተቆጣ።

"ሁላችሁም ወደእኔ፣... አዎ፣ አሪፍ ነው፤... በጣም አኮራችሁኝ፤.." ኮች በአንደኛው /በቀኝ/ እጁ ጠቅልሎ በያዘው የወረቀቶች ጥቅል የሌላኛውን /የግራ/ እጁን መዳፍ እየደበደበ/እያጨበጨበ/ ደስታው በመግለጽ ንግግሩን ጀመረ።

"...ነገርግን አሁንም ቢሆን ማስተካከል ያሉብን ነገሮች አሉ። ለምሳሌ --"

ኮቹ ምሳሌውን ገና ሳይጀምር ተጫዋቾቹ ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው ተነስተው፣ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል ወደተነሳው ጠብ/ድብድብ አቅጣጫ እየጮሁ ከነፉ።

"...ምንድን ነው?!...ወዴት ነው!?... አትመለስም? ና ተመለስ ብዬሃለው! እያንዳንድሽ ተመልሰሽ፣ አሁኑኑ... ፣ እያንዳንድሽ ... ተመልሰሽ እኔ ቡድን የምትገቢ መስሎሻል! ... አንተን እኮ ነው! ..አንተ ..."

ኮች በከንቱ ደከመ፤ የሚሰማ የለ፤ የሚመልስ የለ፤ የሚመለስም የለ።

"...በለው!...በለው...!"

" ያዘው...እንዳትለቀው...በለው!...በለው...!"

ክሽ...ኳ..ከሽ...

ድብድቡ ወደለየለት የሰፈር ብጥብጥ ተቀየረ፤ ቀድሞም በነፍስ የሚፈላለጉ የሁለት ሰፈር ጎረምሶች።

"... እንዴ..እንዴ... ኧረ ፍየላችን!...ወይኔ ፍየላችንን!"

" ወይኔ-ኔኔኔ...ፍ-የ-!"

[ምጽ]

ያንን:

ዲማውን /የቀይ ዳማውን/፣

ጥቅጥቅ ያለውን፣

ጠብደሉን፣

አንበሳ የመሰለውን፣...

ቆለጥ-አልባውን ፍየል

ከተቃራኒው ቡድን ደጋፊዎች መካከል አንዱ ትከሻው ላይ ተሸክሞ ወደራሱ ሰፈር አቅጣጫ ይፈረጥጣል።

ሌሎቹ የ'ሱ ሰፈር ልጆች ከእሱ ኋላ ሆነው፣ ፊታቸውን እነሱን እየተከተሉ የጓደኞቻቸውን የልፋት ውጤት ለማስመለስ ወደሚያሳድዷቸው ወደ'ነ ዛክ /ወደባለሜዳው/ ሰፈር ልጆች አዙረው፣ በዱላና በድንጋይ ናዳ እየተፋለሙ እና እየተከላከሉ አጅበውት ይከተሉታል።

You've reached the end of published parts.

⏰ Last updated: Sep 15, 2022 ⏰

Add this story to your Library to get notified about new parts!

Green SparklesWhere stories live. Discover now